
ግሎባል ባንክ ኢትዮጵያ እና ቀርጫንሼ ግሩፕ ያላቸውን ጠንካራ ስትራቴጂክ አጋርነት አጠናክሮ በማስቀጠል ለጋራ ስኬት በጋራ እንደሚሰሩ ተገለፀ፡፡
ይህ የተገለፀው ባንካችን “ግሎባል ቱር” በሚል መሪቃል እያካሄደ ያለውን የደንበኞችን የስራ እንቅስቃሴ የመጎብኘት እና የውይይት መርሃ ግብር ህዳር 9 ቀን 2019 ዓ.ም በቀርጫንሼ ግሩፕ ባካሄደበት ወቅት ነው፡፡
በጉብኝት መርሃ ግብሩ የግሎባል ባንክ ኢትዮጵያ ተ/ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሳህለሚካኤል መኮንን (ዶ/ር) ፣ ቺፍ ኦፊሰሮች እና የዲፓርትመንት ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
ቀርጫንሼ ግሩፕ በተለያዩ የስራ ዘርፎች በተለይም በግብርና፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ አስመጭና ላኪ፣ በኮንስትራክሽን፣ በትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ እንዲሁም በሆቴል አገልግሎት ዙሪያ እየሰራ እንደሚገኝ ያመላከቱት የግሩፑ መስራችና ዋና ስራ አስፈፃሚ እስራኤል ደገፋ (ዶ/ር) ግሩፑ ለሀገራችን ኢኮኖሚ ዕድገት የበኩሉን አስተዋፅዖ እያበረከተ ይገኛል ብለዋል፡፡
ግሩፑ የግሎባል ባንክ ኢትዮጵያ ደንበኛ ብቻ ሳይሆን ባለአክሲዮን ጭምር መሆኑን የተናገሩት ዋና ስራ አስፈፃሚው ከባንኩ ጋር ያለውን መልካም የስራ ግንኙነትና አጋርነት ይበልጥ በማሳደግ በጋራ ለመስራት ቁርጠኞች መሆናቸውን አመላክተዋል፡፡



ባንካችን በሀገር ኢኮኖሚ ግንባታ ላይ ጉልህ ሚና ካላቸው ተቋማት ጋር ያለውን ስትራቴጂክ አጋርነት በማስፋት ለጋራ ስኬትና እድገት በትብብር የመስራት አካሄዱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለጹት ደግሞ የባንካችን ተ/ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሳህለሚካኤል መኮንን (ዶ/ር) ናቸው፡፡
ቀርጫንሼ ግሩፕ ከባንኩ ጋር ለበርካታ ጊዜያት ሲሰራ መቆየቱን ያወሱት ተ/ስራ አስፈፃሚው፣ በቀጣይም በሀገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ያላቸውን ለቀርጫንሼ ግሩፕ እና መሰል ተቋማት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ በማስቀጠል ለጋራ ዕድገት መስራት እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡
በውይይቱ የሁለቱን ተቋማት የቆየ አጋርነት ወደሌላ ምዕራፍ ማሻገር የሚያስችሉ ሀሳቦች ተነስተው ጥልቅ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
ግሎባል ባንክ ኢትዮጵያ
ለጋራ ስኬታችን