
ግሎባል ባንክ ኢትዮጵያ የደንበኞቹን ፍላጎት መሠረት ያደረገ ሁሉን አቀፍ የባንክ አገልግሎት በመላው የሀገራችን ክፍል እየሰጠ መሆኑን የባንኩ ቺፍ ኮርፖሬት ባንኪንግ ኦፊሰር አቶ ሳኅለሚካኤል መኮንን ገለፁ።
አቶ ሳኅለሚካኤል ይኸን ያሉት “ግሎባል ቱር” በሚል መሪቃል በአሶሳ ከተማ ከሚገኙ ደንበኞች ጋር ሰኔ 26 ቀን 2017 ዓ.ም በአሶሳ ከተማ በአደረጉት የውይይት መርሃ ግብር ነው።
በባንኩ እና በደንበኞች መካከል እንደ ድልድይ የሚያገናኘው “ግሎባል ቱር” የተሰኘው መርሃግብር ባንኩ ለደንበኞቹ ያለውን አወንታዊ አመለካከት የሚያንፀባርቅ መሆኑን ቺፍ ኦፊሰሩ በንግግራቸው አመላክተዋል።
የደንበኞች ግንኙት መምሪያ ዳይሬክተር አቶ መሠረት አሰፋ በበኩላቸው ባንኩ ይበልጥ ወደ ደንበኞቹ እየቀረበ መሆኑን ገልፀው በቀጣይም ከደንበኞች ጋር የሚደረግ ውይይት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በውይይት መርሃ ግብሩ የተሳተፉ የአሶሳ ከተማ የንግድ ማህበረሰብ ክፍሎች በበኩላቸው ከተማዋ ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ እንደሚካሄድባት አውስተው ባንኩ ቅርንጫፍ ከፍቶ አገልግሎት መስጠቱ እንደሚበረታታ ተናግረዋል።



ግሎባል ባንክ ኢትዮጵያ በክብር ጠርቶ አብረን ልንሰራባቸው በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ እንድንወያይ በማድረጉ ደስተኞች መሆናቸውን የገለፁት የውይይቱ ተሳታፊዎች ከባንኩ ጋር አብረው ለመስራትም ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል።
ግሎባል ባንክ ኢትዮጵያ ለጋራ ስኬታችን በሚል መሪ ቃል እንደሚታወቅ ያወሱት አቶ ሳኅለሚካኤል መኮነን ይህን ተግባራዊ ለማድረግም ደንበኞቻችን ብቻ ሳትሆኑ የባንኩ ባለቤት ጭምር በመሆን ለጋራ ዕድገት በጋራ መስራት እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
ግሎባል ቱር ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ተወስኖ ይካሄድ የነበረ ሲሆን የደንበኞችን ሀሳብ እና አስተያየት በማዳመጥ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት እንዲያስችል በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ከሚገኙ ደንበኞች ጋር ውይይት እየተደረገ ይገኛል።
ግሎባል ባንክ ኢትዮጵያ
ለጋራ ስኬታችን!