
ግሎባል ባንክ ኢትዮጵያ ምርት እና አገልግሎቱን እንዲሁም የአሰራር ልህቀቱን ከደንበኞች ጋር የሚያስተዋውቅበት ግሎባል ቱር የተሰኘውን የውይይት መርሐግብር ነሐሴ 10 ቀን 2017 ዓ.ም በሀዋሳ ከተማ ከሚገኙ ደንበኞች ጋር በሴንተራል ሆቴል አከናውኗል።
ባንኩ ከዚህ በፊት ይስተዋሉ የነበሩ የአሰራር ክፍተቶችን በማስተካከል ተወዳዳሪነቱን ይበልጥ በማጠናከረ ለደንበኞቹ ምቹ እና ቀልጣፍ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ለውይይቱ የመነሻ ሀሳብ ያቀረቡት የደንበኞች ግንኙነት መምሪያ ዳይሬክተር አቶ መሰረት አሰፋ ባቀረቡት ሰነድ አመላክተዋል።
በቀረበው የመነሻ ሀሳብ አስተያየታቸውን የሰጡት ተሳታፊዎች ከግሎባል ባንክ ኢትዮጵያ ጋር በትብብር በመስራታቸው በበርካታ መለኪያዎች ውጤታማ መሆናቸውን ገልፀዋል።
የውይይት መድረኩ በመዘጋጀቱ ደስተኞች መሆናቸውን የገለፁት የባንኩ ደንበኞች በቀጣይ ቢስተካከል ያሏቸውን ሀሳብ እና አስተያየቶች ለባንኩ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች አቅርበዋል።
የደንበኞቻችን ስኬታ የግሎባል ባንክ ኢትዮጵያም ስኬት መሆኑን በውይይቱ ወቅት የገለፁት የኮርፖሬት ባንኪንግ ቺፍ ኦፊሰር አቶ ሳኅለሚካኤል መኮነን ለደንበኞችና ባለድርሻ አካላት ለስኬታቸው መዳረሻ ባንካችን ብርቱ አጋር መሆኑን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የደንበኞችን ሀሳብ እና አስተያየት በማድመጥ ክፍተቶችን ማረም እና ጥንካሬዎችን ማስቀጠል የውይይት መድረኩ ዓላማ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የሪቴል ባንኪንግ ቺፍ ኦፊሰር አቶ ውብሸት ዘገየ ናቸው።



የአገልግሎት አሰጣጣችን በማዘመን በደንበኞች ዘንድ የመጀመሪያ ተመራጭ እንዲሆን ያላሰለሰ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አቶ ውብሸት ገልፀዋል።
የግሎባል ባንክ ኢትዮጵያ መስራች እና ከፍተኛ ባለድርሻ የሆኑት አቶ አባተ ኪሾ በበኩላቸው ይኸን መሰል ውይይቶች መዘጋጀታቸው ባንኩ ለደንበኞቹ ያለውን አወንታዊ አመለካከት ያንፀባርቃል ብለዋል።
የስም እና የአርማ ለውጥ መደረጉ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን የገለፁት የማርኬቲንግ እና ኮምዩኒኬሽንስ ዳይሬክተር አቶ ቢኒያም ፍቃዱ በበኩላቸው ይህ ለውጥ ከተደረገ በኋላ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ባንክ እንድንሆን አስችሎናል ብለዋል።
የባንኩን ተወዳዳሪነት ፋይናንስ ነክ በሆኑና ፋይናንስ ነክ ባልሆኑ መለኪያዎች መመዘን እንደሚቻል ያወሱት አቶ ቢኒያም የስም እና የአርማ ለውጥ ከተደረገ በኋላ በሀገር እና በአህጉር አቀፍ ደረጃ የተለያዩ እውቅናና ሽልማቶችን ግሎባል ባንክ ኢትዮጵያ እየተቀበለ መሆኑን ገልፀዋል።
ዘመኑ ከዚህ በፊት የነበሩ አሰራሮችን እየቀየረ እና ወደ ዲጅታል እያመራ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የዲጅታል ባንኪንግ ዳይሬክተር ወ/ሮ መቅደስ በቀለ ናቸው።
ባንካችን ከዲጅታል አንፃር ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የገለፁት ወ/ሮ መቅደስ በቅርቡ በሀገር አቀፍ ደረጃ የመጀመሪያ የሆነ ዲጅታል የአረቦን መድህን ሽፍን ከሌሎች ተቋማት ጋር በመተባበር እየሰጠ ነው ብለዋል።
ደንበኞቻች ለሚፈልጉት የውጭ ምንዛሬን በተመለከት ምላሽ የሰጡት የዓለምአቀፍ ባንኪንግ ዳይሬክተር አቶ እስክንድር ዳባ ደንበኞች የሚያቀርቡትን መረጃ መሠረት በማድረግ የውጭ ምንዛሪ እየተሰጠ መሆኑን አመላክተዋል።
ባንኩ ከደንበኞች ጋር የሚያደርገው ውይይት የሚበረታታ መሆኑን የገለፁት የውይይቱ ተሳታፊዎች ውይይቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
ብሔራዊ ባንክ በአስገዳጅነት ያስቀመጠውን የ5 ቢሊየን ብር የተከፈለ ካፒታል ከተቀመጠው የጊዜ ገደብ አስቀድሞ ማሟላት መቻሉን የገለፁት የባንኩ ከፍተኛ ኃላፊዎች፤ ባለድርሻ አካላት ለሚጠይቁት ተጨማሪ አክሲዮን ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
በውይይት መድረኩ የኮርፖሬት ባንኪንግ ቺፍ ኦፊሰር አቶ ሳኅለሚካኤል መኮነን፣ የሪቴል ባንኪንግ ቺፍ ኦፊሰር አቶ ውብሸት ዘገየ እንዲሁም የባንኩ ዳይሬክተሮች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል።
የባንኩን ምርት እና አገልግሎት ለማስተዋወቅና ለደንበኞች ጥያቄ ፈጣን መፍትሄ ለመስጠት ኢላማ በማድረግ እየተካሄደ የሚገኘው ግሎባል ቱር የተሰኘው የውይይት መድረክ በቀጣይም በተለያዩ ከተማወች እንደሚካሄድ ይጠበቃል።
ግሎባል ባንክ ኢትዮጵያ
ለጋራ ስኬታችን!