
ስብሰባው ለተከታታይ ሁለት ቀናት የባንኩ የቦርድ እና የማኔጅመንት አባላት በተገኙበት በኖራ ሪዞርት ተካሂዷል።
በምክክር መርሃ ግብሩ የባንኩ የመጀመሪያ መንፈቅ ዓመት አጠቃላይ አፈፃፀም እና የበጀት ዓመቱ ከመጠናቀቁ በፊት ሊሰሩ በሚገቡ የስራ አቅጣጫዎች ዙሪያ ውይይት ተደርጓል።
ግሎባል ባንክ ኢትዮጵያ በባንክ ኢንዱስትሪው ተወዳዳሪነቱን ይበልጥ እያጠናከረ እንደሚገኝ የገለፁት የባንኩ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ዮሴፍ ጌታቸው፤ በሁሉም መለኪያዎች ተወዳዳሪነቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በቀጣይ ወራት እንዲከወኑ የተቀመጡ የስራ አቅጣጫዎች ተግባራዊ እንዲሆኑ አሳስበዋል።
የብድር እና የቁጠባ አገልግሎትን ማሳደግ፣ የዲጂታል ባንኪንግ አገልግሎቶችን ማሻሻል፣ የአገልግሎት ጥራትን ከፍ ማድረግ እና የሰራተኞች የመፈፀም ብቃትን ማጠናከር በቀሪ ወራት ትኩረት ተደርጎ ከሚሰራባቸው ዘርፎች መካከል መሆናቸውን አቶ ዮሴፍ በውይይቱ ወቅት ገልፀዋል።
ግሎባል ባንክ ኢትዮጵያ እያስመዘገበ ያለው የስራ አፈፃፀም የሚበረታታ መሆኑን የጠቀሱት የባንኩ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር ተስፋዬ ቦሩ በበኩላቸው በቀጣይ ወራትም በዲጂታል ባንኪንግ፣ በደንበኛ ተኮር አገልግሎት እና በአፈፃፀም ብቃት ላይ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት የተጀመረውን የዕድገት ጉዞ ማጠናከር ይገባል ብለዋል።



ዕቅዶች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ እና ጥራት እንዲከወኑ የተለመደው ድጋፍ እና ክትትል ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ዶ/ር ተስፋዬ ተናግረዋል።
ባንኩ የዲጂታል አገልግሎቶቹን እያስፋፋ ከመሄዱ ጋር በተየያዘ የደንበኞችን መረጃ ጥበቃ፣ የመረጃ ቴክኖሎጂ ደህንነት እና የቅርንጫፍ ደህንነት ስርዓቶችን ማጠናከር ላይ ልዩ ትኩረት እየተደረገ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የባንኩ ምክትል የቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር ዮናስ ሀጎስ ናቸው።
የላቀ የሳይበር ደህንነት ስርዓቶችን በሁሉም የዲጂታል ባንኪንግ አገልግሎቶች ላይ በመዘርጋታችን ደንበኞች በባንካችን ላይ ያላቸው እምነት ይበልጥ እንዲጠነክር ማስቻሉንም ዶ/ር ዮናስ ገልጸዋል።
የስብሰባው ተሳታፊዎች በበኩላቸው በቀጣይ አምስት ወራት ውስጥ ባንኩ ባስቀመጣቸው ዋና ዋና የአፈፃፀም መለኪያዎች መሠረት አመርቂ ውጤት ለማስመዝገብ ቁርጠኞች መሆናቸውን ተናግረዋል።
በባንክ ኢንዱስትሪው ውስጥ የሚገኙ መልካም ዕድሎችን በአግባቡ መጠቀም የሚያስችሉ የተለያዩ ስትራቴጂዎች እና የስራ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ የምክክር መርሃ ግብሩ ተጠናቋል።
ግሎባል ባንክ ኢትዮጵያ
ለጋራ ስኬታችን!