
የግሎባል ባንክ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለአክሲዮኖች ባንኩ የተጣለበትን ሀገራዊ እና ማህበራዊ ኃላፊነት በተሟላ ሁኔታ ተወጥቶ የተቋቋመበትን ዓላማ እውን እንዲያደርግ ከምንጊዜውም በላይ አብረው እንደሚሰሩ ገለፁ።
የባንኩ ከፍተኛ ባለአክሲዮኖች ይኸን የገለፁት ከባንኩ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ነሐሴ 15 ቀን 2018 ዓ.ም በባንካችን ዋና መ/ቤት ውይይት በአካሄዱበት ወቅት ነው።
በባንኩ ማኔጅመንት እና በባለአክሲዮኖች መካከል ቀጣይነት ያለው የመረጃ ልውውጥ እና የቅርብ የሥራ ግንኙነት እንዲኖር ማድረግ፣ የአሰራር ዘመናዊነትን እና ዲጂታል የባንክ አገልግሎቶችን በማስፋፋት የባንኩን አጠቃላይ የገበያ ድርሻ እና የትርፍ ህዳግ ማሳደግ እንዲሁም የኮርፖሬት አስተዳደር መርሆችን በማጠናከር ባለአክሲዮኖች በባንኩ የረጅም ጊዜ እቅዶች ላይ ንቁ ተሳታፊ የሚሆኑበትን ስርዓት መዘርጋት የውይይቱ ዋና ዓላማ መሆኑን የባንካችን ተ/ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሳኅለሚካኤል መኮንን ገልጸዋል፡፡



ባለአክሲዮኖቹ ባንኩ በፋይናንስ ኢንዱስትሪው ውስጥ ያለውን ተወዳዳሪነት ይበልጥ ለማጠናከር እና የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞውን ለማፋጠን ለሚያደርጋቸው ጥረቶች ሁሉ ከጎኑ ለመሰለፍ ቁርጠኞች መሆናቸውን በውይይቱ ተናግረዋል።
ባለአክሲዮኖች ለባንኩ የሚያደርጉት የማያቋርጥ አጋርነት ባንኩ ላስመዘገበው ስኬት ትልቅ መሰረት መሆኑን በውይይቱ ወቅት የገለጹት አቶ ሳኅለሚካኤል፤ በቀጣይም የባንኩን አጠቃላይ አፈፃፀም ይበልጥ ለማሳደግ እና የባለአክሲዮኖችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትጋት እንሰራለን ብለዋል፡፡



የባለአክሲዮኖች ያልተቆጠበ ድጋፍ፣ የደንበኞች እምነት፣ የባንኩ አመራሮች ቁርጠኝነት እና የሠራተኛው ትጋት ተቀናጅተው ግሎባል ባንክ ኢትዮጵያ የላቀ ስኬቶችን ለማስመዝገብ እና የረጅም ጊዜ ራዕዩን እውን ለማድረግ ትልቅ ምዕራፍ እንደሚከፍት በውይይቱ ወቅት ተገልጿል።
በባንኩ ውስጥ የነበሩ የአሰራር ክፍተቶችን ከስር ከመሰረቱ በማክሰም ባንኩ ስኬታማ፣ ባለአክሲዮኖችም ውጤታማ እንዲሆኑ ከምንጊዜውም በላይ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል ተብሏል፡፡
ከባንካችን ባለአክሲዮኖች ጋር የሚደረገው ወይይት በቀጣይም ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡
ግሎባል ባንክ ኢትዮጵያ
ለጋራ ስኬታችን