
ግሎባል ባንክ ኢትዮጵያ በመጀመሪያው መንፈቅ ዓመት በተለያዩ የስራ መለኪያዎች የላቀ አፈፃፀም ላስመዘገቡ በመቐለ እና አካባቢው ለሚገኙ ቅርንጫፎች ታኅሳስ 23 ቀን 2018 ዓ.ም በፕላኔት ሆቴል የዕውቅናና የምስጋና መርሃ ግብር አካሂዷል።
በበጀት ዓመቱ በመጀመሪያው ስድስት ወራት የሚበረታታ ስራ መከወኑን በዕውቅና መርሃ ግብሩ ወቅት የገለፁት የምዕራብ አዲስ አበባ ዲስትሪክት ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ግርማ፤ በሁለተኛው መንፈቅ ዓመትም ሁሉም ቅርንጫፎች ከዚህ የተሻለ አፈፃፀም እንዲሚያስመዘግቡ ያላቸውን እምነት ተናግረዋል።
ግሎባል ባንክ ኢትዮጵያ በመጀመሪያው መንፈቅ ዓመት በበርካታ መለኪያዎች አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን የገለፁት አቶ ሰለሞን ባንኩ ከዕቅድ በላይ እንዲያሳካ ዕውቅና የተሰጣቸው ቅርንጫፎች እና ሰራተኞች አይነተኛ ሚና መውሰዳቸውን ተናግረዋል።
ዛሬ የተካሄደው የዕውቅናና የምስጋና መርሃ ግብር ቅርንጫፎች በሁለተኛው ግማሽ ዓመት ከመጀመሪያው የተሻለ አፈፃፀም እንዲያስመዘግቡ አወንታዊ ሚና እንደሚያበረክትም ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።
ዛሬ የተከናወነው የዕውቅና መርሃ ግብር የባንካችን ስኬት በቡድን ሥራ፣ የተሳለጠ አመራር በሚሰጡ የስራ ኃላፊዎችና የላቀ የባንክ አገልግሎት በመሰጠቱ የመጣ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የማርኬቲንግና ህዝብ ግንኙነት ስራ አስኪያጅ አቶ ተመስገን ፍቃዱ ናቸው።



የላቀ አፈፃፀም አስመዝግበው ዕውቅና የተሰጣቸው ቅርንጫፎች ስራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ያሳሰቡት አቶ ተመስገን ዛሬ ዕውቅና ያላገኙ ቅርንጫፎች በሁለተኛው ግማሽ ዓመት ጠንክረው በመስራት ዕውቅና ከሚሰጣቸው ቅርንጫፎች መካከል እንዲሆኑ መስራት አለባቸው ብለዋል።
ከሁሉም ሰራተኞች ጋር በመሆን በሙሉ ዓቅም እየሰሩ መሆንን የገለፁት ዕውቅና የተሰጣቸው የቅርንጫፍ ስራ አስኪያጆች በበኩላቸው ባንኩ ርዕዩን እንዲያሳካ ከምንጊዜውም በላይ ተግተው እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
ግሎባል ባንክ ኢትዮጵያ በሁለተኛው መንፈቅ ዓመት የላቀ አፈፃፀም እንዲያስመዘግብ ከዋናው መስሪያ ቤት የሚደረገው ክትትል እና ያልተቆጠበ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በዕውቅና መርሃ ግብሩ ወቅት ተነግሯል።
ዛሬ በተከናወነው የዕውቅና መርሃ ግብር አዲግራት፣ መቐለ እና አዲሓቂ ቅርንጫፎች በትግራይ ክልል ካሉ ቅርንጫፎች መካከል የላቀ አፈፃፀም በማስመዝገብ ዕውቅና ከተሰጣቸው ቅርንጫፎች መካከል ናቸው።
የላቀ አፈፃፀም ላስመዘገቡ ቅርንጫፎች የሚሰጠው የዕውቅናና የምስጋና መርሃ ግብር በአዲስ አበባ ለሚገኙ ቅርንጫፎችም መሰጠቱ ይታወቃል።
ግሎባል ባንክ ኢትዮጵያ
ለጋራ ስኬታችን!