
ግሎባል ባንክ ኢትዮጵያ ፋይናንስ ነክ በሆኑና ባልሆኑ መለኪያዎች በደንበኞች ዘንድ የመጀመሪያ ተመራጭ እና ምርጡ ባንክ እንዲሆን ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የባንኩ ቺፍ ሪቴል ባንኪንግ ኦፊሰር አቶ ውብሸት ዘገዬ ገለፁ፡፡
ቺፍ ኦፊሰሩ ይህን ያሉት ግሎባል ባንክ ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ወራት የላቀ አፈፃፀም ላስመዘገቡ ቅርንጫፎች እና ሰራተኞች የዕውቅናና የምስጋና መርሃ ግብር ታኅሳስ 14 ቀን 2018 ዓ.ም በሀያት ሪጀንሲ ሆቴል ባካሄደበት ወቅት ነው፡፡
ግሎባል ባንክ ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ወራት በበርካታ መለኪያዎች አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን የተናገሩት የባንኩ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ይህ እውን እንዲሆን የባንኩ አመራሮች እና ሠራተኞች የአንበሳውን ድርሻ ወስደዋል ብለዋል፡፡
የባንኩ ያለፉት አምስት ወራት የስራ አፈፃፀም የሚበረታታ መሆኑን ያወሱት የስራ ኃላፊዎቹ በቀጣይም የነበሩ ጠንካራ ጎኖችን ይበልጥ በማጠናከር፤ ይስተዋሉ የነበሩ ክፍተቶችን ደግሞ በማክሰም በበጀት ዓመቱ መጠናቀቂያ ከዕቅድ በላይ ማከናወን እንደሚጠበቅ አፅንዖት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
እ.ኤ.አ በ2035 በአገልግሎት ልህቀት በምስራቅ አፍሪካ ከሚገኙ ባንኮች መካከል ግንባር ቀደም መሆን የባንኩ ራዕይ መሆኑን የገለፁት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ራዕዩን እውን በማድረግ በሁለንተናዊ መመዘኛዎች ምርጡ ባንክ እንዲሆን የላቀ አፈፃፀም የሚያስመዘግቡ ሠራተኞች እና አመራሮች እንዲበራከቱ ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል፡፡



ግሎባል ባንክ ኢትዮጵያ በፋይናንስ ኢንዱስትሪው ተወዳዳሪነቱ እየጨመረ መሆኑን የገለጹት የማርኬቲንግና ኮምዩኒኬሽንስ ዳይሬክተር አቶ ቢኒያም ፍቃዱ፤ በቀጣይም በሁለንተናዊ ዘርፍ ተወዳዳሪ በመሆን በደንበኞች ዘንድ የመጀመሪያ ተመራጭ ባንክ እንዲሆን የተለያዩ ስራዎች እየተከወኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተሰጣቸው የዕውቅናና የማበረታቻ ሽልማት ደስተኞች መሆናቸውን የገለጹት የቅርንጫፍ ስራ አስኪያጆች በበኩላቸው፤ በቀጣይም ከዚህ የበለጠ በመስራት ከዕቅድ በላይ ለመፈፀም ያልተቆጠበ ርብርብ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡
በዕውቅናና በምስጋና መርሃ ግብሩ ቺፍ ሪቴል ባንኪንግ ኦፊሰር አቶ ውብሸት ዘገዬ፣ ቺፍ ፋይናንስና ሰፖርት ኦፊሰር አቶ ዳሳ ጎቤ፣ ቺፍ ኮርፖሬት ባንኪንግ ኦፊሰር አቶ ሳኅለሚካኤል መኮንን፣ ቺፍ አይ ቲ ኦፊሰር አቶ ሲሳይ አየለ፣ የባንኩ ዳይሬክተሮች እና የቅርንጫፍ ስራ አስኪያጆች ተገኝተዋል፡፡
የእውቅናና የምስጋና መርሃ ግብሩ የቀጣይ ስራዎችን አቅጣጫ በማስቀመጥ ተጠናቋል፡፡
ግሎባል ባንክ ኢትዮጵያ
ለጋራ ስኬታችን!